የሚወለዱበት፣ የሚሞቱለትና የሚሞቱበት መሬት መስፍን ወልደ ማርያም
የሚወለድበትን መሬት ማንም ሰው አይመርጥም፤ የዘመኑ ቅንጦት ኢትዮጵያ አርግዞ አሜሪካ መውለድ ቢሆንም፣ ልጁ ምርጫው ውስጥ የለበትም፤ አንኳን ልጁ አባትዬውም ምርጫው ውስጥ የሚገባ አይመስለኝም፤ በእንደዚህ ያለው ኢትዮጵያን አስጠልቶ-ሌላ-እንዲሆን በተፈጠረ ቅንጦት የሚወለድ ኢትዮጵያዊ ምን እንደሚሆን መተንበይ ያዳግታል፤ ልጁ ወይም ልጅቱ በራሳቸው ዝንባሌ፣ ፍላጎትና ጥረት ከኢትዮጵያ ጋር ያላቸው ግንኙነት በእልህ ከአልተለወጠ እናቶቻቸው የተለሙላቸው ማንነት ከኢትዮጵያዊነት ይገነጥላቸዋል፤ ነገር ግን የኢትዮጵያዊነት ስሜት እንዲህ በቀላሉ ተቀርፎ የሚወድቅ አይደለም፤ ሲደንቀኝ የቆየ ነገር ልናገር፤ አንድ ጊዜ በኢሰመጉ ተልእኮ ካናዳ ሄጄ አንድ ስብሰባ ላይ አንድ አርመን ወጣት ነበረ፤ ይህ ሰው ለኢትዮጵያ ያለው ስሜት በጣም የጋለ ነበር፤ በሌላ ዘመን ደግሞ ፋጡማ ሮባ በአትላንታ ማራቶን በአሸነፈች ጊዜ ደግሞ በቴክሳስ የሚኖር ከአንድ ግሪክ ገንፍሎ የወጣው ንግግር በጣም ልብን የሚነካ ነበር፤ ለዚህ አርመንና ለዚህ ግሪክ የኢትዮጵያዊነት ስሜት በዘር የተላለፈላቸው አይመስለኝም፤ ስለዚህም አሜሪካ የሚወለዱትም ኢትዮጵያውያን ልጆች እናቶቻቸው ሳያውቁ ከውስጣቸው የሚያስተላልፉላቸው ስሜት ኢትዮጵያዊነታቸውን ይገነባው ይሆናል፤ እንደሚመስለኝ የሚሞቱለት መሬት ከውስጥ ከነፍስ ጋር በተገናኘ ስሜት የተቆራኘ ነው፤ መሬቱንና ስሜቱን ምን አገናኛቸው? ምን አቆራኛቸው? እንዴት ተቆራኙ? የሚሉትንና ሌሎችንም ጥያቄዎች ለመመለስ መሞከር እዚህ ቦታው አይደለም፤ ለዚች መሬት የሞቱላት በሚልዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች መኖራቸውን አምነን በመቀበል እንነሣ፤ ምናልባትም አብዛኛዎቹ ቁራጭ መሬትም አልነበራቸውም፤ እንዲያውም አብዛኞቹ ለመቃብር ያህል ሁለት ክንድ መሬት አንኳን አላገኙም፤ በተሰለፉበት ወድ...