የአፍሪካ ነገር – የኢትዮጵያ ነገር መስፍን ወልደ ማርያም
በሃያኛው ምዕተ-ዓመት ላይ የታወቀ የፈረንሳይ ፈላስፋ ነበረ፤ እሱ የዩኒቨርሲቲ ተማሪ በነበረበት ጊዜ ከእሱ ጋር በዩኒቨርሲቲ ሁለት አፍሪካውያን አብረውት ይማሩ እንደነበሩ ይናገራል፤ እነዚህ አፍሪካውያን የፈረንሳይኛ ቋንቋን ልክ አንደፈረንሳዮች እየተናገሩ፣ እንደፈረንሳዮች እያሰቡ ከፈረንሳዮቹ ተማሪዎች ጋር እኩል በትምህርት እየጎለበቱ ነበር፤ በኋላ እነዚህ አፍሪካውያን ወደአገራቸው ተመልሰው ሥልጣን ላይ ሲወጡ ሰፊ አገራቸው ለሁለቱ የተማሩ አፍሪካውያን የማይበቃ ሆነባቸው፤ ስለዚህም አንደኛው የአገር መሪ ሆነና ሌላውን ገደለው፤ የፈረንሳዩ ፈላስፋን ያሳዘነው ትዝብት ነው። በአለፉት ሃምሳ ዓመታት ውስጥ በአፍሪካ የታየው የሥልጣን ሽኩቻ ለብዙ የአፍሪካ አገሮች የእድገት ማነቆ ሆኖ ቆየ፤ ከአውሮፓውያን ቄሣራዊ ኃይሎች ቅኝ አገዛዝ ነጻ ሲወጡ ከፍተኛ ተስፋ የተጣለባቸው አገሮች ዛሬ ቆመው ቀርተዋል፤ በሰሜን አፍሪካ አልጂርያና ቱኒስያ እንደፈረንሳይ የሚቆጠሩ ናቸው ይባል ነበር፤ እነዚህ ትልልቅ አገሮች ለሁለት ለሁለት ሰዎች የማይበቁ ሆነው የመከራ አገሮች ሆነዋል፤ ከፈረንሳይ ጋር በአደረጉት መራራ ትግል ሕዝቦቹ የከፈሉትን መስዋእትነትና ትግላቸው አሳድሮባቸው የነበረውን የላቀ ተስፋ መሪዎቹ ዋጋ አልሰጡትም፤ (ተመስገን ደሳለኝ በፋክት ቁጥር 33 ‹‹የሕወሓት ሰማዕታት አጭር ማስታወሻ፣) በዚህም ምክንያት እነሱ ለአንድ ወንበር ሲፎካከሩና ተወዳዳሪዎቻቸውን አስረውም ሆነ ገድለው ወንበሩን ለብቻቸው ሲይዙት ቆይተዋል። በአንድ በኩል ከወንበሩ በሚመነጨው ኃይልና ሀብት መከታን የሚያገኙ መስሏቸው በነበራቸው ተስፋ፣ በሌላ በኩል በምዕራባውያን ኃይሎች ላይ ተማምነው ሕዝባቸውን በመናቃቸው በአረብ አገሮች መሪዎች ላይ በቅርቡ በተከሰተው ወረርሺኝ ብዙዎች ከወንበራቸው ተደፍተዋል፤ የሁ...