ሐተታ አድዋ በ በእውቀቱ ስዩም
የአድዋ ድልን ከድንበር ሉአላዊነት ጋር አያይዞ መተንተን የተለመደ ነው፡፡ ድሉ አነሠ በዛ የሚለው ጭቅጭቅ ከዚህ መሠረት ይፈልቃል፡፡ በኔ ግምት የአድዋ ድል ትልቅ ጭብጥ ‹‹የሰውነት ክብር›› ይሰኛል፡፡ ቀደምቶቻችን ወደ አድዋ የጋለቡት በግፍ የተነጠቁትን የሰውነት መታወቂያ ለማስመለስ ነው፡፡ እንዲያውም ሰው መሆናቸውን በማያዳግም መንገድ ያረጋገጡት አድዋ ላይ ነው ማለት ይቻላል፡፡ ወገኖቼ!! ሰው መሆንን ማረጋገጥ ቀላል ነገር አይምሰላችሁ፡፡ አባቶቻችን ከአውሮፓውያን ጋር የሚጋሩትን ግን ደግሞ ከአውሮፓውያን ቀድመው የሚያውቁትን ቅዱስ መጽሐፍ ጠቅሰው ሁላችንም ያዳም ልጆች ነነ ይሉ ነበር፡፡ እና ያዳም ልጆች ነነ ብለው የሚያምኑ ፈረንጆች ቢቸገሩ የሚደርሱላቸው፣ ቢጠቁ የሚታደጓቸው ወንድሞቻቸው እንደሆኑ ያስቡ ነበር፡፡ በርግጥም የሃይማኖት አንድነት የቀለም ልዩነትን ደምስሶ አዳማዊ ወንድማማችነትን ያስገኘበት የዘመን ምዕራፍ ነበር፡፡ ክርስቶፈር ደጋማ የተባለ የፖርቹጋል ነፍጠኛ ለኢትዮጵያ ደሙን ያፈሰሰው የማተብ አንድነት ስለገፋፋው ነው፡፡ ይሁን እንጂ ባንድ ወቅት የሚያገለግል የኑሮ ዋስትና በሌላው ዘመን አያገለግልም፡፡ ሁላችንም ያዳም ልጆ ነነ የሚለው የዝምድና ውል ከእለታት አንድ ቀን ያገልግሎት ዘመኑ አለቀ፡፡ በ1548 ተወልዶ በ1600 እንደጧፍ የተቃጠለው ዦርዳኖ ቡርኖ የተባለ የጣልያን መናፍቅ ‹‹ኢትዮጵያውያን ያዳም ልጆች አይደሉም፤ ቅድመ-አዳማዊያን ናቸው እንጂ›› ብሎ ፃፈ፡፡ በቡርኖ ዘመን ኢትዮጵያ የጥቁር ዘር ሁሉ የወል ስሙ ነው፡፡ ቅድመ አዳማዊ ማለት ደሞ በአዳምነት ማዕረግ ያልደረሠ ጅምር ፍጡር ማለት ነው፡፡ ይህ አስተሳሰብ ጥቁሮች በእግዜር አምሳል የተፈጠሩ አይደሉም የሚል ድምዳሜ ላይ ያደርሳል፡፡ ያለማለዘቢያ ለመግለፅ፣ ጥቁሮች ከእንሥሣትና...