ከሰዉ ሀገር ርቆ የተንጠለጠለ ተስፋ… By Fike Man

ሸዋ አረጋን እያጨሰ ነበር ያገኘሁት፡፡ ሁለታችንም የጫነን መኪና ደጀን ላይ እረፍት ያደረገዉ ለቁርስ ነዉ፡፡ እኔ ወደ ትዉልድ መንደሬ ለዓመት በዓል….እሱ የትዉልድ መንደሩን ተሰናብቶ ወደ ስደት ….ወደ ሰዉ ሀገር ….ወደ ሱዳን …ከዚያም ሌላ ስደት…..

ሲጋራ አጫጫሱ የነገር ስለመሰለኝ ሲጋራ የምታጨስ አትመስልም አልኩት ፈገግ ብዬ

ሸዋ ፊቱን ቅጭም እንዳደረገ “ማለት ?” አለኝ

እኔም አይ ነገር የምታጨስ ስለመሰለኝ ነዉ፡፡ በጭሱ መሀል መከፋትህ ይታያል፡፡ ፊትህም ልክ አይደለም አልኩት፡፡

እንዲህ የተጀመረዉ ዉይይታችን ቀጥሎ “የመገናኛ ልጅ እንደሆነ ፣ ከአዲስ አባባ ወጥቶ እንደማያዉቅ፣ትምህርት ጨርሶ ስራ እንዳጣ፣የሴቶች የዉበት ሳሎን ተመርቆ ስራዉን ቢቀጥልም ሕይወት በዝግመት ከመሄድ እንዳልተፋታች፣ሁለቱእህቶቹ በአረብ ሀገር ፣ ወንድሙ ሱዳን ኑሮን ለማሸነፍ እንደተሰደዱ ሆኖም ግን ጠብ የሚል ነገር እንደጠፋ ……እሱም እንደ እህትና ወንድሞቹ ለስደት ቀልቡን እንደሰጠና መጀመሪያ ወደ ሱዳን ከዚያ ሌላ ስደት እንዳሰበ” አጫወተኝ

የምለዉ አልነበረኝም ብቻ ዝም ከምል ብዬ ታዲያ ዓመት በዓልን ከማለቴ አላስጨረሰኝም

“እናቴ ባይሆን በዓልን አብረን እንዋል ስትለኝ እንባዋ ምንም ያልመሰለኝ ኑሮ እስኪበቃኝ ስላስነባኝ ነዉ፡፡ በዓል ዝም ብሎ አለ እንዴ? ዛሬ ከትናንት በኑሮ ደረጃ ባይሆን እንካን በተስፋ ደረጃ ካልተሻለ መኖር ምንድን ነዉ?” እያለ ራሴን ሲያፋጥጠኝ

እኔም ጭጭ ብቻ የሀመልማል ሙዚቃ ትዝ አለኝ

“በድን አካል ይዞ ልቡን ያሸፈተዉ፡
ፊቱን አይመልስም ተስፋ እስካካልሸተተዉ፡
ሃሳብ ያዘመተዉ ሰዉ፡፡
የእኔ ነዉ የሚለዉ አንድም ነገር ሲያጣ
ለምን አይሰደድ ሰዉ ከሃገሩ አይወጣ”

እናቱም በተደጋጋሚ ትደዉላለች “የት ደረስክ? ምግብ በላህ ?” ይህ ጥያቄ ምን አልባት ድንበር እኪሻገር ይሆናል፡፡ ድንበር ከተሻገረማ በምን አድራሻ ይገኛል? ስደተኛ ምን አድራሻ አለዉ አድራሻዉ የትም ነዉ፡፡

ነገሩን ይባስ ግራ የሚያደርገዉ መኪናዉን የሚያሽከረክረዉ ሾፌር ከጎኑ ለተቀመጠዉ ሰዉዬ መኪናዉን እንዴት እንደገዛት ሲገልፅ “መመህር እንደነበር፣ በተለያዬ ቢሮዎች ሃላፊ ሆኖ እንደሰራ፣ ከሌሎች ዉጫጭ ካድሬዎች ጋር እንብላ ሲሉት አልበላም ብሎ ተጣልቶ እንደወጣ፣ ሌሎች 8 እና 9 ቦታ ሱሉልታ ላይ ሲቸበችቡ እሱ 2 መሬት ብቻ ሽጦ ለመኪናዋ መነሻ እንደሆነዉ” ደረቱን ነፍቶ ሲናገር ነዉ፡፡

ሌባ የሚኖርባት ሀቀኛ የሚሰደድባት ሃገር ከእኛዋ ጉድ ዉጭ ወዴት ይገኛል ……ከማለት ዉጭ ምን ይባላል?

ሾፌሩ መተርተሩን አላቆመም “አሁን ሀገሪቱ የተሻለ ደረጃ እንዳለች፣ በተለይ መለስ ዜናዊ ባይሞት የትና የት እንደምትደርስ” ሲናገር ለቅንጣት ታህል እንካ ሸዋ አረጋ ለእኔ ሲያወራልኝ የነበረዉን እዉነታ ያዳመጠ አይመስልም፡፡

ኢዮብ ለካ በመከራ ወራቱ ወዶ አይደለም “እኔ በጨለማ ዉስጥ መኖሬን እያወኩ ወዳጆቼ ሌሊቱ አልፎ ፀሀይ ወጥታለች ይሉኛል” ያለዉ::

Comments

Popular posts from this blog

መግለጫ በኢትዮጵያ፡ ትናንት እና ዛሬ By Zelalem Kibret

Ethiopian editor questioned over story on Azeb Mesfin