በቆብ ላይ ሚዶ (ሁለት) ፤ ትምህርትና ተማሪ ቤት (መስፍን ወልደማርያም)
የዛሬዎቹ ባለሥልጣኖች በደርግ ጊዜ አልነበሩም፤ የደርግን ስሕተት በማየት አልተማሩም፤ ትምህርታን አቋርጠው
ወደጫካ የገቡት ከትምህርት የሚበልጥባቸው ምኞት አጋጥሟቸው ነው፤ የትምህርት ገዜያቸውን በጫካ ባለሥልጣን በመሆን፣
እነሱው ሕግ አውጪና ዳኛ፣ እነሱው የጫካ አስፈጻሚ ሆነው ቀዩ፤ ደርግ በጠራራ ጸሐይ የሚሠራውን እነሱ በጫካ ጭለማ
ሲሠሩ ቆዩ፤ በሥልጣን ላይ ከወጡ በኋላም በጣም ቆይተው ትምህርት አስፈላጊ መሆኑን በትንሹ ተገነዘቡ፤ በጣም የተማሩ
ሰዎች ጋር ሲገናኙ ማፈር አስጨነቃቸው፤ ስለዚህም ቀላሉ ነገር የተማሩ ሰዎችን አለማቅረብ፣ ትምህርታቸውን
በጠባያቸው ካላጠቡ የተማሩ ሰዎች ጋር በቀር አለመገናኘት፣ እንዲያውም የትምህርትን ዋጋና ጥራት በማዋረድ አዲስ
የሚመረቁት ሁሉ ለባለሥልጣኖች አንገታቸውን የሚደፉ ዓይነት እንዲሆኑ ማድረግ ዓላማ ሆነ።
የተማሩና የሠለጠኑ የጦር መኮንኖችም ተሸናፊዎች በመሆናቸው ትምህርታቸው ዋጋ እንደሌለው ማረጋጋጫ እያደረጉ የወያኔ መሪዎች በአደባባይ ተናገሩ፤ ትንሽዋ ቢምቢ ሰውን መግደል እንደምትችል ያልተገነዘቡት ከጫካ የመጡ ሰዎች በመግደል ማሸነፍን የትምህርትን ዋጋ-ቢስነት ማረጋጋጫ አደረጉት፤ የተማሩ ሰላማዊም የጦር መኮንኖችም ዋጋ-ቢስነታቸው ኑሮአቸውን በማናጋቱ በችግር ወደሌላ ሥራ ተሰማሩ፤ ወይም አገር ጥለው ተሰደዱ፤ በሰላማዊውም ሆነ በፖሊስና በጦር ሠራዊቱ የተማረ ሰው እጥረት መፈጠሩ ለወያኔ መግቢያና መደላደያ ምቹ ሁኔታን ፈጠረ።
በየትኛውም የሥልጣን ወንበር ላይ ለመቀመጥ ማናቸውም ዓይነት የትምህርት መመዘኛ ተሽሮ ሚዛኑ ስለተሰበረ ማንንም ከሜዳ እያነሡ በተፈለገው ወንበር ላይ ማስቀመጥ እየተለመደ ሄደ፤ በየሚኒስቴሩ ከመከላከያ ጀምሮ እስከአገር አስተዳደርና የውጭ ጉዳይ ወንበሮች ላይ የተደለደሉት ሁሉ ችሎታም ሆነ ብቃት ሳይኖራቸው ነበር፤ አንዳንዶች ብልጥ የሆኑት ከዱሮው መንግሥት ባለሥልጣኖች ውስጥ አንገታቸውን ደፍተው ሊሠሩ የሚችሉትን በጓዳቸው አስቀምጠው እንዲሠሩላቸው ያደርጉ ነበር፤ ቀንደኛ የኢሠፓ አባሎች ሳይቀሩ በጓዳ በር ተቀጥረው ነበር፤ በመሠረቱ የተማረ ሰው ለአሽከርነት አይመችም፤ ሆኖም የአሽከርነት ባሕርይ ያለው ሰው ቢማርም ትምህርቱ የባሕርዩን ጉድፍ አያጥበውም፤ አንዳንዶቻችን እንደምናውቀው ለአጼ ኃይለ ሥላሴም፣ ለኮሎኔል መንግሥቱም፣ ለመለስም በተከታታይ ታማኝ እየሆኑ ያገለገሉ ሰዎች አሉ፤ የማይታመኑ መሆናቸውን ያስመሰከሩ ሰዎች የሚታመኑበት አገር ከኢትዮጵያ ሌላ መኖሩን አላውቅም፤ ከኢጣልያ ወረራ ጀምሮ ይህ የእንጀራ ሎሌነት እየተለመደ ብሔራዊ ባሕርይ ወደመሆን እየተጠጋ ነው።
በትምህርትና በተግባር መሀከል ድልድይ የማይገኝለት ገደል ተፈጠረ፤ ትምህርት በሎሌነት! ሎሌ ለመሆን መማር! መማር ሎሌ ለመሆን! ሎሌነት ለአንድ ሰው፣ ሎሌነት ለአንድ ቡድን፣ ሎሌነት ለአንድ እምነት፣ ሎሌነት ለሆድ! አስቡት እንዲህ ያለ ሰው ምን ይማራል? ማን ያስተምረዋል? እንዴትስ ይማራል? ተምሮስ ምን ይሠራል? የተወረሰውን አንጎል ማጣጠብ ይቻል ይሆናል፤ አእምሮን ለሚያንጽ ትምህርት ግን ነጻነት ያለው አስተማሪ፣ ነጻነት ያለው ተማሪ፣ ነጻነት ያለበት መድረክ ያስፈልጋሉ፡፡
የሆነላቸው ባለሥልጣኖች ወደውጭ እየሄዱ ልዩ የአቋራጭ ሥልጠና እየተሳተፉ፣ አለዚያ አስተማሪዎች ለጥቂት ጊዜ እዚሁ መጥተው የአቋራጩን ሥልጠና በአጭር ጊዜ ውስጥ እየሰጡ፤ ‹‹ተማርን›› ብለው ራሳቸውንና ተከታዮቻቸውን አሳመኑ፤ ለምን የውጭ አገር ሰዎች አስፈለጉ? እነሱን ለማስተማር የሚችሉ ኢትዮጵያውያን ባለሙያዎች አልነበሩም ወይ? እነዚህንና ሌሎች ተመሳሳይ ጥያቄዎች አእምሮአቸው ማንሣት ባይችልም ወዳጅ ዘመዶች ሳይነግሯቸው የቀሩ አይመስልም፤ ግን እንዲህ ያለውን ምክር መቀበል አላዋቂነታቸውን ማጋለጥ ስለሚሆን ተቀባይነት ሊኖረው አይችልም!
የትምህርት ጊዜያቸውን ሥልጣንን በማሳደድ ለውጠው ሳይማሩ የቀሩት ከፍተኛ የአገር ገንዘብ ወጪ እያደረጉ በስማቸው ላይ የሚጨምሩት ምልክት የትምህርትን እውነተኛ ፍቺ እንዳልተገነዘቡ የሚያሳይ ነው፤ የትምህርት ማዕርጎች ከቢ.ኤ. ጀምሮ እስከፒኤች.ዲ. የትምህርት ቤት በራፉን ሳይረግጡ በግዢ ሊገኙ ይችላሉ፤ በግዢ የሚገኘው የምስክር ወረቀት እንጂ ትምህርት አይደለም፤ ለመሆኑ ኢትዮጵያን ያህል አገር እያስተዳደሩ የዩኒቨርሲቲ ትምህርት ለመከታተል ይቻላል ወይ? ከተቻለ ወይ አገር መግዛቱ ጨዋታ ነው፤ ወይ ትምህርት የተባለው ጨዋታ ነው፤ ወይም ሁለቱም ጨዋታ ነው፤ ያለትምህርት አገር መግዛት ጨዋታ ነው፤ ያለሥርዓት ትምህርት ጨዋታ ነው፤ ለአዋቂ ሰው በጥንት ነገሥታት ዘመንም ቢሆን ያው ነበረ የሚል ክርክር ማንሣቱ ራስን ያጋልጣልና የሚበጅ አይመስለኝም፤ በቆብ ላይ ሚዶ ጌጥ አይሆንም፤ ጥቅምም የለው፤ ከቆቡ ስር ያለው መላጣ ቢሆንስ!
በትዕቢት የተወጠሩት በአገር ላይ ባለሙሉ ሥልጣን የሆኑት ሰዎች የትምህርትን መሠረታዊ ባሕርይ ስተውታል፤ በመጀመሪያ መደበኛ ትምህርት በተወሰነ የእድሜ ክልል ውስጥ ወደተማሪ ቤት ለብዙ ዓመታት እየተመላለሱ የሚያገኙት እውቀት እንጂ በሥልጣን ወንበር ላይ ተቀምጠው እያዘዙ እንደዕቃ የሚያስመጡት አይደለም፤ መማር ደረጃ በደረጃ አስተማሪዎች የሚሰጡትን ትምህርት ተከታትሎ ፈተናዎችን እያለፉ የሚጓዙበት የእውቀት ጎዳና ነው፤ ትምህርት የአስተማሪና የተማሪ ግንኙነት ነው፤ አስተማሪና ተማሪ ማለት አዋቂና አላዋቂ ማለት ነው፤ በየኔታ(የኔ ጌታ)ና በልጅ መሀከል ነው፤ አስተማሪው የተማሪውን አእምሮ በሕገ ኀልዮት፣ ጠባዩን በሥነ ሥርዓት እየገራ፣ እየተቆጣ፣ እየኮተኮተ የሚያሳድግ ነው።
ትምህርት በተማሪዎች መሀከል ያለ ግንኙነት ነው፤ ተማሪዎችን የሚገራው አስተማሪው ብቻ አይደለም፤ ተማሪዎቹም እርስበርሳቸው አንዱ ከሌላው የሚማረውና የሚገራበት መንገድ ብዙ ነው፤ እርስበርሳቸው እየተቀላለዱ፣ እየተሰዳደቡ፣ እየተራረሙ፣ እየተፎካከሩና እየተገማመቱ የሚያድጉበት ሥርዓት ነው፤ ስለዚህም ተማሪዎች ትምህርት የሚያገኙት ከአስተማሪዎች ብቻ አይደለም፤ ይህ ሁሉ ሁኔታ በሌለበት በሥልጣን ወንበር ላይ ተኮፍሶ በሎሌነት በግል የተቀጠረውን አስተማሪ ወደታች እያዩ መማር የሚቻለው እንዴት ነው? መማር ማለት ወደላይ እያዩ ነው፤ ወደታች እያዩ መማር አይቻልም፤ አንድ ሰው ስለህክምና ምንም ሳይማር አውቃለሁ ብሎ ሥራ ከጀመረና አጉል መድኃኒት እየሰጠ የባሰ ሲያሳምምና አካልን እየቀደደ መልሶ መስፋት ሲያቅተው፣ በኋላ ሕመምተኞቹን አጋድሞ ህክምና ልማር ብሎ አስተማሪ ቢፈልግ ምን ይባላል?
ኢትዮጵያውያን ባለሙያዎች ከኢትዮጵያ ተርፈው ብዙ ሌሎች አገሮችን አዳርሰዋል፤ የወያኔ ሹሞች ግን በከፍተኛ ወጪ ከአሜሪካና ከእንግልጣር የውጭ አገር ሰዎችን ሲያስመጡ የነበረው አንደኛ በኢትዮጵያዊ ተበልጠው ላለመታየት፣ሁለተኛ የአለማወቃቸውን መጠን እንዳይናገር ሹልክ ብሎ ገብቶ ሹልክ ብሎ ሳይታወቅ ቶሎ ወዳገሩ የሚመለስ የውጭ ሰው በማስፈለጉ፣ ሦስተኛ የገንዘብ ችግር ስለሌለ ነው።
ባለሥልጣን ሆኖ አላዋቂ መሆን ያሳፍራል፤ አዋቂ መስሎ አላዋቂ ሆኖ መገኘት የባሰ ያሳፍራል፤ ሳይማሩ በጉልበት ባለሥልጣን መሆን ሰውዬውን ራሱን የሚያሳፍርበት ደረጃ ላይ ደርሰናል፤ ያፈረ ባለሥልጣን በጎ ነገርን አያስብም፤ በየሳምንቱ አንዳንድ ለጆሮ የሚቀፉና አገርንና ሕዝብን የሚጎዱ ነገሮችን እንሰማለን፤ አይታረሙም፤ የሚናገሩት ክፉ ነገር ነገ ክፉ ውጤትን ሊያስከትል እንደሚችል አያውቁም፤ ሥልጣን አፋቸው እንዳመጣ እንዲናገሩ ያስችላቸዋል፤ አለመማራቸው ከዚያች ቅጽበት አልፈው እንዳያዩ ይጋርዳቸዋል።
እድገት የሚመጣው ትምህርት በነጻነት ሲመራና፣ ሥልጣን በሕዝብ ቁጥጥር ሲያዝ ነው፤ ሥልጣን በነጻነት፣ ትምህርት በቁጥጥር የቁልቁለት መንገድ ነው።

Comments
Post a Comment